ጥንስሱ | ቅርጫው | ይስሙ ንጉሥ | አለቃ አጽሜ Vs ግራዝማች ዮሴፍ እና አስገራሚ አሟሟታቸው። Adwa Part 1

2 years ago
2

እ.ኤ.አ የካቲት 16,1986...በኦቶ-ቫን ቢስማርክ (የጀርመኗ በርሊን ቻንሰር) አርቃቂነት "አራጆቹ” የአውሮፓ ቅኝ ገዢዎች ተሰብስበው አፍሪካን እንደ ቅርጫ ከፊታቸው በካርታ ላይ ዘርግተው እና ከበው ሙዳ ሙዳውን ሊዘነጣጥሉ ዕጣ ተጣጣሉባት።

በሰላም ፣ በፍቅር ፣ ከተፈጥሮ ተዋዳ ተዋህዳ ፣ በህብረ-ሰብዓዊነት እና በልዕለ-ሰብዓዊነት ትኖር ወደነበረችው እማማ አፍሪካ ከመጓዛቸው ፣ ከመዝመታቸው እና ከመቀራመታቸው በፊት በበርሊኑ ስብሰባቸው ላይ "ይሄ ላንተ - ያ ለኔ" ተባባሉ ።

(እ.ኤ.አ ከህዳር 15 ቀን 1884-የካቲት 26 ቀን 1885) የተከናወነውን ወሳኝ ስብሰባ ወራሪዎቹ Berlin Conference ሲሉት ፣ ሃቀኛ የታሪክ ምዑራን ግን "አፍሪካን የመቀራመት ጉባኤ" ይሉታል።

አፍሪካን እንደ ቅርጫ ለመቀራመት ያሰፈሰፉት የቋመጡት ሃገራትም 👇

👉ጀርመን
👉ኦስትሮ፣ሃንጋሪ
👉ቤልጅየም
👉ዴንማርክ
👉ፈረንሳይ
👉ብሪታንያ
👉ጣ ልያን
👉ኔዘርላንድስ እና ፖርቹጋል ናቸው።

እዚኽ ጋ አንድ መታወስ ያለበት ወሳኝ ጉዳይ አለ ፣ መላውን አፍሪካ በወረራ በጉልበት ለማስገበር ሲገሰግሱ ፣ በግልፅ ባልታወቀ ምክንያት ኢትዮጵያን በጦር ከማስገበር ይልቅ "እንቃረጣት" ብለው (ብሪታንያ ፣ ፈረንሳይ እና ጣልያን) "Tripartite Agreement " ተፈራርመው ለአፄ ምኒልክ የ "እወቁልን" ጦማር ላኩ።

ይኽም የእወቁልን ጦማር "ልንበላህ ነውና እወቅልን ፣ዝም ብለኽም ተበላልን" አይነት ድፍረት የተቀላቀለበት አይናውጣነት ነው።

፩፪፫፬፭፮፯፰፱፲

ንጉሰ ነገስት አፄ ምኒሊክም "ስለነገራችሁኝ አመሰግናለሁ፣ነገር ግን እኔ በሌለሁበት የተወሰነውን አላውቅም” በማለት መለሱ ፣

ጥልያንም ይኽንን ስትሰማ "ድርሻውን" ቅርጫ ኢትዮጵያን ለመቦጨቅ ሌላ መሰሪ ዘዴ መጠቀም እንዳለባት ወጠነች።

፩፪፫፬፭፮፯፰፱፱

ጣልያን ለወረራ ለቅኝ-ግዛት መንገድ ከፋቹን ውል #Tratto di uccialli ከኢትዮጵያ ጋር በተወካይዋ "አንቶኔ" በኩል በሚያዝያ 25 ,1881 ዓ.ም ተዋዋለች።

#አንቀጽ 17 አማርኛው "ግርማዊ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ከአውሮፓ መንግስታት ጋር ለሚፈልጉት ጉዳይ ሁሉ በኢጣልያ በኩል ማድረግ ይችላሉ" የሚልና የኢትዮጵያን መልካም ፍቃድ የሚያከብር ሲሆን ፣

ጣልያንኛው "ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገራት ጋር የምታደርጋቸው ማንኛውም ግንኙነት በጣልያን በኩል ይሆናል" የሚል አስገዳጅነት ያለው አንቀጽ ነው።

፩፪፫፬፭፮፯፰፱፲

ለመሆኑ የዚኽ ጦሰኛ ውል የትርጉም ልዩነት ምስጢር እንዴት ሊታወቅ ቻለ? የጣልያንኛውን እና አማእኛውን የትርጉም ልዩነትስ ማን ተረዳው፣

የአድዋ ድል ሲነሳ እና ሲወሳ ፣ ለአድዋ ድል አስተዋጽኦ ያደረጉ እልፍ አእላፍት ከአራቱ የኢትዮጵያ ማህዘናት ከሰሜን ከደቡብ ከምስራቅ የተወጣጡ እና ለድሉ በግንባር ከመዋደቅ ፣በሃሳብ የጦርነት ዘዴ መወጠን ብሎም ትጥቅ እና ስንቅ ማቀበል ድረስ ለድሉ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ኢትዮጵያውያንን መርሳት ተገቢ አይደለም።

ከነዚኽም መካከል በውጫሌ ውል ዙሪያ የውሉ ትርጓሜ ላይ እና ምስጢሩን መፍታት ላይ ወሳኝ ሚና በመጫወታቸው ሊነሱ የሚገባቸው ሁለት ሰዎች አሉ 👇

አንደኛው ግራዝማች ዮሴፍ
ሁለተኛው አለቃ አፅመ ጊዮርጊስ ናቸው።

ለዲፕሎማሲ ሲሉ ንጉሰ ነገሥት አፄ ምኒልክ ቀደም ብለው የጣልያንን አፍ እንዲያጠኑ ደጃዝማች መኮንን የተባሉ ሰውን እና ግራዝማች ዮሴፍን ወደ አውሮፓ ልከዋቸው ነበር፡፡

በውጫሌ ውል ላይ ወሳኝ ሚና የነበራቸው ግራዝማች ዮሴፍ ትውልዳቸው ከትግራይ ሲሆን በምፅዋ የካቶሊክ ሚሲዮን ት/ቤት ስለተማሩና የውጭ ሃገር ቋንቋ በመልመዳቸው

፩ኛ - ለንጉሱ በአስተርጓሚነት አገልግለዋል።
፪ኛ - ምኒሊክ ከፈረንሳይ መንግስት ጋር ወዳጅነት እንዲያጠነክሩ በማድረግም የጦር መሳርያ እንዲያገኙ አግዘዋል።

ከዚኽም በበለጠ ለአድዋ ጦርነት መንስኤ ነው የሚባለውን የውጫሌ ውል ( ከፈረንሳይኛ ወደ አማርኛ ) ተርጉመው ለንጉሡ አቅርበዋል ፣

ነገር ግን የግራዝማች ዮሴፍ ትርጉም ላይ ሆን ተብሎ ሳይሆን የትርጉም ስህተት እንዳለው አለቃ አፅመ ጊዮርጊስ በተባሉ ሊቅ ታወቀ።

አለቃ አጽመ ጊዮርጊስ ( የምንይልክ ሰላይ ፣ አረብኛ ፣ ፈረንሳይኛና ላቲን ቋንቋ ተናጋሪ፣ የኦሮሞ ታሪክ መፅሀፍ ደራሲና እጅግ ሊቅ ነበሩ።

"አለቃ አጽመ ጊዮርጊስ ወትም አጽሜ የሸዋ ተወላጅ ሲሆኑ ፣ የታሪክ ጸሐፊ በዘመኑ ከነበሩ ሊቆች ዋነኛው ነበሩ።
አለቃ አጽሜ በታሪክ ከሚታወሱበት ነገሮች አንዱ የውጫሌ ስምምነት ከተፈፀመ በኋላ አንቀፅ 17 ላይ ግራዝማች ዮሴፍ የትርጉም ስህተት እንደፈጸሙ በመጠቆማቸው ነበር ይህንንም ለአፄ ምኒልክ ያሳሰቡት አለቃ አጽሜ ነበሩ።

ይህን የትርጉም ልዩነት ከሌሎች ሰምተው አማርኛ ጣልያንኛ እና ፈረንሳይኛውን ካስመረመሩ በኋላ የተረዱት እቴጌ ጣይቱም
"ይስሙ ንጉሥ ፣ እኔ ሴት ነኝ ፣ ጦርነት አልወድም ። ከዚህ መሳይ ውል ግን ጦርነት እመርጣለሁ..."  በማለት ከተናገሩ በኋላ

ከፊታቸው በፍርሃት ቆሞ ያደምጣቸው ለነበረ ሶላቶ የጥልያን ተላላኪ በቁጣ እንዲኽ አሉት

" ሂድ የዛሬ ሳምንት አድርገው...መንገዱን ጨርቅ ያርግልህ...ባሻህ ጊዜ ተመለስ ተሰናድተን እንጠብቅሃለን"

"የኢትዮጵያን ሰው ባታውቀው ነው ለሃገሩ መሞት ማለት ለሃበሻ ጌጡ ነው።" በማለት እልህና ቁጭት በተቀላቀለበት ቅላፄ ጥልያኑን አስደንብረው ለሚመጣው ኹሉ ዝግጁ እንደሆኑ ቁርጡን ገልጸው ወደ ሃገሩ ሲሄድ የሰማውን ይኽንኑ እንዲናገር ነገሩት።

{ከውጫሌ ከተማ 18 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ያለና ውሉ የተፈረመበት ቦታም የዚኽን ታሪካዊ ዳራ በመላበስ #ይስማ ንጉሥ ተባለ እስከዛሬም በዚኽ ስሙ ይጠራል }

፩፪፫፬፭፮፯፰፱፲

የሚገርመው የግራዝማች ዮሴፍ ትርጉም ስህተት እንደነበረው ሲደረስበት ግራዝማቹን ለማሳጣት እና ለማሳነስ ብሎም ከንጉሱ ከባድ ቅጣት እንዲጣልባቸው ከኢጣልያ በኩል አንቶኒ ግራዝማቹን ተጠያቂ ለማድረግ ስድብ ጀመረ ፣

ጣይቱም "ቢያጠፋስ አሽከራችን ነው እኛ እንቀጣዋለን አንተ መሳደብ የለብህም" በማለት በግራዝማች ዮሴፍ ላይ ከ ሶላቶው የሚሰነዘሩባቸውን ትችቶች ንግስቲቱ ተከላከሉላቸው።

ሳላምቤኒ የግራዝማችን ጭንቀት በወቅቱ ሲገልፅ " በዚህ ነገር የታመመ የከሳ ዓይኑ ጎድጉዶ የሚታየው ዮሴፍ ነበር።" ብሏል

ግራዝማች ዮሴፍ ሆን ብለው ሳይሆን ከፅሁፍ ይልቅ እውቀታቸው ንግግሩ ላይ መሆኑ ስለታመነ ስህተታቸው ታርሞ ግራዝማች ተብለው ኃላ ሩስያ ተልከዋል።

ግራዝማች ዮሴፍ ሃገራቸውን በጦር ሜዳም አገልግለዋል ፣ የጦርነቱን ሂደትና ጀብድ በፈረንሳይኛ እየፃፉ አዲስ አበባ በመላክ ታሪኩ ለኛ እንዲደርሰን አድርገዋል፡፡

ንጉሱ እና ንግስቲቱ በጣልያኑ ሰው ተታለው ግራዝማች ዮሴፍ ሆን ብለው የትርጉም ስህተት እንዲኖር እንዳደረጉ ቆጥረው ሃገር ከድተዋል ብለው አስበው እስከሞት የሚያደርስ ቅጣት ቢቀጧቸው ኖሮ ግራዝማች ዮሴፍ ስህተታቸው ከታረመ በኋላ ለሃገራቸው በጦር ሜዳ ብሎም በፈረንሳይኛ ፕሮፓጋንዳ እና የአድዋን ታሪክ በመፃፍ ያበረከቱትን በርካታ አስተዋጽኦ ልናገኝ አንችልም ነበር።

ደጃዝማች ዮሴፍ ሌላው በታሪክ የሚታወሱት በአስገራሚው አሟሟታቸው ነው ፣

ጥይት ሳይነካቸው ከተመለሱ እድለኞች አንዱ ሲሆኑ መሃል ከተማ ከገቡ በኃላ መጠኑ የበዛ ኮሶ ጠጥተው ተኙ...አልነቁምም።

ሃገሬው እንዲኽ የሚል ቅኔ ለእኚኽ ዥግና ተቀኝቶላቸዋል 👇

እንዴት ያለ ዥግና ከጦር ሜዳ ተረፈ፣
በሞተ በሬ ግን ተሸነፈ፡፡

ክብረት ይስጥልን ግራዝማችና አለቃ!!

ኢትዮጵያ ብረሣሽ ቀኜ ትርሣኝ ባላስብሽም ምላሴ ከጉሮሮዬ ትጣበቅ።

(ነጽሩ ወዘሠናየ አጽንዑ)

==================ይቀጥላል==============

Loading comments...