ዘመነ ብርሀን

2 months ago
139

ዘመነ ብርሃን
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የዘመን አከፋፈል መሰረት ከጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በፊት ከታህሳስ 13 እስከ ታህሳስ 21 ቀን ያለው ዘመን
ዘመነ ስብከት ይባላል፡፡
ነቢያት የነፍሳችን ብርሀን ይወለዳል ብለው ስለመስበካቸው፣እውነተኛ ብርሀን ይመጣል ብለው ስለማስተማራቸው የሚታሰብበት ሲሆን በዚሁ ኢየሱስ ክርስቶስ አማናዊ ብርሀን መሆኑ ይሰበካል፤ይዘመራልም፡፡
በዘመነ ብሉይ መከራ ሥጋ፣ መከራ ነፍስ የጸናበት የሰው ልጅ ብርሃን ከሆነው አምላክ ጋር የተራራቀበት ስለነበር ነቢያት ያሉበትን ያንን ዘመን ጨለማ ብለው በመግለጥ የነፍሳችን ብርሀን ይወለዳል፣ እውነተኛ ብርሃን ይመጣል ብለው ስለመስበካቸው የሚታሰብበት ቀን
/ሳምንት/ ነው።
በዚህ ሳምንት ከልደተ ዳዊት እስከ ፍልሰተ ባቢሎን የነበረው 14 ትውልድ ይታሰብበታል፡፡

ልበ አምላክ ክቡር ዳዊት በመዝሙሩ   አምላክ ወልደ አምላክ ብርሀን ስለመሆኑ <<ብርሃንህንና ጽድቅህን ላክ>>
መዝ፦ 42፥3 በማለት ይጸልይ ነበረ፡፡ ይህም ብርሃን፣ ጽድቅ፣ እውነት የሆነውን ልጅህን (ወልድን) ላክልን፤እርሱ መርቶ ወደ መንግሥተ ሰማያት ያስገባን ዘንድ ማለት ነው።
ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ 
<<ለሰው ሁሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃን ወደ ዓለም መጣ>> ብሎ እንደመሰከረው እውነተኛ ብርሀን ስለሆነው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሀንነት የሚሰበክበት ሰንበት ነው›
ዮሐ፦1፥1-11፡፡
ጌታችንም በመዋዕለ ስብከቱ 
<<እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ፤ የሚከተለኝ የሕይወት ብርሃን ይሆንለታል እንጂ በጨለማ አይመላለስም>> ዮሐ፦ 8፥12 ብሎ እንዳስተማረው በዚህ ሰንበት ስለ እርሱ ብርሀንነትና ክርስቲያኖችም እርሱን ብርሀናቸው እንዲያደርጉት ይሰበካል፡፡
በዚህ ዕለት
<<ከብርሀን የተገኘ ብርሀን>> እንዲሁም <<የማይነገር ብርሃን>> የተባለ ኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ ብርሃን መሆኑ ይሰበካል፡፡ <<ብርሃን ወደ ዓለም መጣ>> እየተባለ በቅዱስ ያሬድ መዝሙር ይመሰገናል።

እኛም አባቶቻችንን አብነት አድርገን ቅዱስ ኤፍሬምም በሰኞ ውዳሴ ማርያም እንዳሰተማረን <<በዚህ አለም ለሚኖሩ ሰዎች ሁሉ የምታበራ እውነተኛ ብርሀን ስለሰው ፍቅር ወደ አለም የመጣህ፤ ፍጥረት ሁሉ በመምጣትህ ደስ አለው፡፡ አዳምን ከስሕተቱ አድነኽዋልና፡፡ ሔዋንንም ከሞት ጻዕረኝነት ነጻ አድርገኃታልና። የምንወለድበትን መንፈስ ሰጠኽን፤ ከመላዕክት ጋርም አመሰገንህ>> በማለት የሕይወታችን ብርሀን የሆነውን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እናመሰግናለን፡፡

Loading 1 comment...