የመላዕክት አሰፋፈር

18 days ago
17

በሶስቱ ዓለመ መላዕክት ከከፋፈላቸው በኋላ መላዕክቱን በአስሩ የመላዕክት ከተሞች ማለትም
በኢዮር ያሉት በአራቱ የመላእክት ከተሞች
በራማ ባሉት በሦስቱ የመላዕክት ከተሞች
በኤረር ባሉት በሦስቱ የመላዕክት ከተሞች
በነገድ በነገድ አሰፈራቸው አፀናቸው
እንዴት ነው ቢሉ

1 በኢዮር
1.1 ነገደ አጋእዝት
1.2 ነገደ ኪሩቤል
1.3 ነገደ ሱራፌል
1.4 ነገደ ኃይላት

2 ራማ
2.1 ነገደ አርባብ
2.2 ነገደ መናብርት
2.3 ነገደ ሥልጣናት

3 ኤረር
3.1ነገደ መኳንንት
3.2 ነገደ ሊቃናት
3.3 ነገደ መላእክት

1 በኢዮር
1.1 ነገደ አጋእዝት
የመጀመሪያዎቹን በኢዮር ያሰፈራቸውን የመላእክት ነገዶች አጋእዝት ብሎ ጠራቸው፡፡
አለቃቸውን ሳጥናኤልን አድርጐ ሾመላቸዋል፡፡
በኋላም ሣጥናኤል አምላክነትን ሽቶ ከክብር በመውረዱ ቅዱስ ሚካኤል ተረክቦታል፡፡
ሣጥናኤል ማለት ቅሩበ እግዚአብሔር አኃዜ መንጦላእት፣ አቅራቤ ስብሐት ማለት ነው፡፡

ሳጥናኤል ከክብሩ ሳይዋረድ ለመጀመሪያው ነገድ አለቃ ነበረ።  የመጀመሪያ የክብር ስሙ 
<<ሳጥናኤል>> ነው።

ሲክድ ስሙም ተወሰደበትና 
ዲያብሎስ 
(ፈታዌ፤ አምላክና አምላክነትን ፈላጊ፣ዖፍ ሰራሪ፤ለማሳት የሚፋጠን በራሪ ወፍ፣ጋኔን፤ ዕቡይ፣ ትዕቢተኛ፣ ውዱቅ፤ የተጣለ፣ ሰይጣን፤ ባለጋራ፣ ከሳሽ) የሚባሉና ግብሩን የሚገልጹ ስሞች ተሰጡት፡፡

ታሪክ
ፈጣሪያችን እግዚአብሔር መላእክትን ፈጥሮ በተሰወራቸው ጊዜ አእምሯቸው ጠያቂ አገናዛቢ ስለሆነ <<ማን ፈጠረን? ከየት መጣን?>> << በራስ በራሳችን ተፈጠርን? ወይስ ከሌላ ነው?>>እያሉ እርስ በእርሳቸው ሲጠያየቁ በቦታና በመዓርግ ታላቅ የነበረው ሳጥናኤል ማንም ሳያሳስተውና ሳይመክረው ሐሰትን ለመጀመሪያ ጊዜ ከልቡ (ከአእምሮው) አንቅቶ <<እኔ ፈጠኋችሁ>> ብሎ በድፍረት ተናገረ። ዮሐ፦፰፥ ፵፬።
ይህን ሰምተው << ሰጊድ ይገባዋል>>
ያሉ አሉ።።<< እኛም እንደ እርሱ ነን>>
ያሉም አሉ።<<አምላክ ነኝ ያለስ ከእርሱ በቀር ሌላ የለምና ፥ ይሆንን? >>ብለው የተጠራጠሩ አሉ።ሀልዎተ እግዚአብሔርን ሳይመረምሩ የቀሩም አሉ።
እኲሌቶቹ ግን ፦ <<በምን ፈጠርኋችሁ ይለናል፥ በቦታ ከበላይ በመሆን ፈጠርኋችሁ እንዳይለን ፥ እኛ የበታቾቻችንን መቼ ፈጠርናቸውና ነው?። በዚያውስ ላይ ምቀኞቹ አይደለንም፤ በእውነት ፈጣሪ ከሆነ ፈጥሮ ያሳየን።>> ብለው፦ <<ፈጥረህ አሳየን>> አሉት። እርሱም እፈጥራለሁ ብሎ ፥ እጁን ወደ እሳት ቢጨምር ፈጀውና <<ዋይ>> አለ። በዚህን ጊዜ <<በአፍአ ያለውን (የሚነገረውንና እና የሚሠራውን ብቻ የሚያውቅ) አምላክ ቢሆን ነው እንጂ ውሳጣዊውን (ልብ ያሰበውን የሚያውቅ) አምላክ ቢሆን ኖሮ ገና ሳስበው ለምን አሰብከው ፥ ባለኝ ነበር ፤>> አለ። ወዲያው ልቡን ተሰማውና <<ዋይ>> አለ። እግዚአብሔር ግን ፈወሰው። ይህንንም ማድረጉ ንስሐ ቢገባ እንደሚምረው ሲነግረው ነበር።

ከዚህ በኋላ በመላእክት ሽብር ቢጸናባቸው ቅዱስ ገብርኤል 
<<ንቁም በበኅላዌነ እስከንረክቦ ለአምላክነ>>
የፈጠረን አምላካችንን እስክናገኘው (እስኪገለጥልን) ድረስ በያለንበት እንጽና
በማለት ብሎ ባረጋጋቸው ጊዜ በመላእክት መካከል መለያየት ተፈጠረ፤ይህም ዲያብሎስ በመላእክት መካከል የዘራው የመጀመሪያ መከፋፈል ነው።ማቴ፦፲፫፥፳፰
በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር <<ብርሃን ይሁን>>ብሎ ብርሃንን ፈጠረ።ዘፍ፦፩፥፫
ብርሃን በተፈጠረ ጊዜ ሳጥናኤል ምንም መፍጠር የማይችል የሐሰተኛ አምላክ መሆኑ ተገለጠበት።በስሕተቱም ተፀፅቶ ሊመለስ ስላልቻለ ቅዱሳን መላእክት በሰልፍ (በጦርነት) ተዋግተው መዓርጉ ተነጥቆ ከነበረበት የክብር ቦታ ከመንግሥተ ሰማያት ከነሠራዊቱ (ከነተከታዮቹ) ወደ ጥልቁ ተጥሏል። ራእ፦፲፪፥፮ ፤ ኢሳ፦፲፬፥፲ ፤ ይሁ፦፩፥፲፫

1.2 ነገደ ኪሩቤል
በዕብራይስጥ<<ኪሩቤም>> ይባላሉ።
በሁለተኛው ከተማም ዐሥሩን ነገደ ኪሩቤል ብሎ ከሰየማቸው በኋላ ኪሩብ የተባለውን መልአክ አለቃ አድርጐ ሾመላቸው፡፡
እነዚህም የቀሳውስት አምሳል ናቸው፡፡
ሕዝ 1÷6-7
ሕዝ 10÷1
<<እኔም አየሁ፣ እነሆም በኪሩቤል ራስ ላይ ባለው ጠፈር በላይቸው እንደ ስንፔር ድንጋይ ያለ እንደዙፋን የሚመስል መልክ ተገለጠ>> እንዲል፡፡
እነዚህንም ከወገባቸው በታች አንድ ከወገባቸው በላይ አራት አድርጐ ፈጥሯቸዋል፡፡ እነዚህም አራት ገፅ
ገፀ ሰብእ፣ ገፀ አንበሳ፣ ገፀ ንስር፣
ገፀ እንስሳ (ላም) ይባላሉ በሌላ
አጠራር <<አርባእቱ እንሰሳ>> በመባል የምንጠራቸው ናቸው፡፡ከእግራቸው እስከ ራሳቸው በዓይን የተሸለሙ ናቸው፡፡ እነዚህ ኪሩቤል እንደነብር ዡንጉርጉር አንድም እንደመስታወት ብሩህ ናቸው፡፡

1.3 ነገደ ሱራፌል
ሱራፌል የሚለው ቃል በዕብራይስጥ
<<እሳት>> <<እሳታውያን>> የሚል ትርጉም ይኖረዋል።
በሦስተኛው ከተማም ዐሥሩን ነገደ ሱራፌል ብሎ ሰየማቸው፡፡ እነዚህም የዲያቆኖት አምሳያ ናቸው፡፡ አፈጣጠራቸውም ስድስት ክንፍ አድርጐ ፈጥሯቸዋል፡፡
ኢሳ፦6÷2
<<ሱራፌል ከእርሱ በላይ ቆመው ነበር ለእያንዳንዱም ስድስት ክንፍ ነበረው በሁለት ክንፍ ፊቱን ይሸፍን ነበር በሁለቱም ክንፍ እግሮቹን ይሸፍን ነበር፡፡ በሁለቱም ክንፍ ይበር ነበር>> እንዲል የእነኚህም አለቃቸው ገፀ ንስር፣ ገፀ እንስሳ ነው ስሙም ሱራፊ መልአክ ይባላል፡፡

1.4 ነገደ ኃይላት

በዐራተኛው ከተማም ዐሥሩን ነገድ ስማቸውን ኃይላት አላቸው፡፡
እነዚህ የሥላሤ ሰይፍ ጃግሮች፣ሰይፋ ያዦች ናቸው፡፡
የኃይላት አለቃቸው ቅዱስ ሚካኤል ሲሆን እነዚህንም ከነአለቃቸው በኢዮር በዐራተኛው ሰማይ አስፍሯቸዋል፡፡
ሲሆንእነዚህመላእክትበሰይጣንፈተና
 
እነዚህ መላዕክት በሰይጣን ፈተና ለደከሙ ሰዎች ኃይል እና ብርታትን
የሚሰጡ የሰይጣን ሰራዊትም በደከሙት ላይ ኃይላቸውን እንዳይጠቀሙና እንዳይጎዷቸው የሚያደርጉ ናቸው፡፡
ከዚህ በተጨማሪ እነዚህ መላእክት በየገዳማቱ እና በየምድረ በዳው በተጋድሎ የሚኖሩትን የሚያጸኑና የሚያበረቱ
የመላእክት ወገን ናቸው፡
1ኛ ጴጥ፦3፥22

ከላይ የቀጠለ፦
2 ራማ
2.1 ነገደ አርባብ
<<ረበበ>> ማለት <<ጋረደ>> ማለት ሲሆን
<< አርባብ>> ማለት << የሚጋርዱ>>
<<የሚሸፍኑ>> ማለት ነው።
የመጀመሪያዎቹን በራማ ያሉትን ዐሥሩን ነገደ መላእክት አርባብ ብሎ ከሰየማቸው በኋላ አለቃቸውን ቅዱስ ገብርኤል መልአክ አድርጐ ሾመላቸው፡፡
አገልግሎታቸው የስላሴን መንበር የሚጋርዱ፣የሚሸፍኑ ወይም ዘወትር በዙፋኑ ፊት የሚቆሙ ናቸው።
ሉቃ፦1፥19
ከዚህ በተጨማሪ ዘወትር ከሚወረወረው የሰይጣን ፍላፃ ያመልጡ ዘንድ የሰው ልጆችን የሚሸፍኑ፣የሚጋርዱ ናቸው።
መዝ፦90፥10-12

2.2 ነገደ መናብርት
መናብርት ማለት ነበረ(ተቀመጠ) ከሚለው ግስ የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም
<<ተቀማጮች>> ማለት ነው።
ከዚህ በኋላ በራማ ያሉትን ሁለተኛዎቹን ዐሥሩን ነገደ መላዕክት ስማቸውን መናብርት አላቸው።
አለቃቸው ቅዱስ ሩፋኤል መልአክ
አድርጎ ሾመላቸው።

እነዚህ መላዕክት ረቂቅ የሆኑ የመብረቅ
ጋሻን የተጎናጸፍ የእሳት ጦርን የያዙ አነፋስም ይልቅ የፈጠኑ መላዕክት ናቸው።
አገልግሎታቸውም ለእግዚአብሔር የምክሩ አበጋዞች እና የምስጢሩ ጋሻ ጃግሬዎች ናቸው።

2.3 ነገደ ሥልጣናት
ከዚህ በኋላ በራማ ያሉትን ሦስተኛዎቹን
ዐሥሩን ነገደ መላዕክት ስማቸውን
ሥልጣናት አላቸው።
አለቃቸው ቅዱስ ሱርያል መልአክ
አድርጎ ሾመላቸው።
የሥላሴ ነጋሪት መቺዎች፣ትጉሀን መላዕክትም ለቅዳሴ የሚያተጉ ከመሆናቸው በተጨማሪ በዝናባት እና በብርሃናት ላይ ሥልጣን ተሰጥቶአቸዋል።

ከዚህ በተጨማሪ
የሰው ልጆች ከፅድቅ ሲርቁ በክፋትም ሥራ ቢጸኑ በእግዚአብሔር ፈቃድ የተለያዪ መቅሰፍቶችን የሚያመጡ ለዚህም ከአምላካቸው ዘንድ ሥልጣንኑ ያላቸው
መላዕክት ናቸው።
በዚህ በተቃራኒው በንስሐ ተመልሰው አምላካቸውን በተሰበረ መንፈስ ምህረትን
የሚለምኑን በምልጃቸው  ከአምላክ ዘንድ
እርቅን የሚያመጡ መላዕክት ናቸው።
2ኛ ተሰ፦1፥7

3 ኤረር
3.1ነገደ መኳንንት
<<መኳንንት>> ማለት አለቆች፣ገዢዎች ሹመኞች ማለት ነው።
የመጀመሪያዎቹን በኤረር ያሉትን ዐሥሩን ነገደ መላእክት መኳንንት ብሎ ከሰየማቸው በኋላ አለቃቸውን ሰዳክያል መልአክ አድርጐ ሾመላቸው፡፡
እነዚህም የሥላሴ ቀስተኞች ናቸው፡፡
ተራራ የሚንድ ድንጋይ የሚሰነጥቅ የእሳት ፍላፃ የእሳት ቀስት ይዘው ሰውን ሁሉ ከመከራ ሥጋና ከመከራ ነፍስ የሚጠብቁ ናቸው፡፡
በተጨማሪም በትንሣኤ ዘጉባኤ የሰውን ሁሉ አጥንት የሚሰበስቡና ምድርን ለምጽአት እንዲያዘጋጁ የሚላኩ ናቸው፡፡
ማቴ፦24፥30

3.2 ነገደ ሊቃናት
ከዚህ በኋላ በኤረር ያሉትን ሁለተኛዎቹን ዐሥሩን ነገደ መላእክት ስማቸውን ሊቃናት አላቸው፡፡
አለቃቸውም ሰላትያል መልአክ አድርጐ ሾመላቸው፡፡
እነዚህም የሥላሴ የፈረስ ባልደራስ ናቸው፡፡በእሳት ፈረስ ተቀምጠው የእሳት ልብድ ተለብደው፣ በከዋክብት አምሳል የብርሃን ሰላጢን ይዘው በልባቸው የሚሳቡ፣በእግራቸው የሚሽከረከሩትን፣ በክንፋቸው የሚበሩትን በደመ ነፍስ ሕያዋን የሆኑትን ሁሉ የሚጠብቁ ናቸው፡፡

3.3 ነገደ መላእክት
መላዕክት የሚለው ስያሜ ምንም
እንኳ ለሁሉም የተሰጠ ቢሆንም
በተለየ መልኩ በመጨረሻ ማዕረግ ላይ ላሉ ነገደ መላእክት የተሰጠ ስም ነው።
ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር አምላክ በኤረር ያሉትን በሦስተኛ ከተማ አድርጐ ዐሥሩን ነገድ መላእክት ብሎ አስፍሯቸዋል፡፡ አለቃቸውም አናንኤል መልአክ አድርጐ ሾመላቸው፡፡
እነዚህ እንደ ብረት የጸና የእሳት ነጐድጓድን ወደምድር የሚወነጭፉ፣ የፀሐይን፣ የጨረቃን፣ ከዋክብትን፣ እዝርዕትን፣ አትክልትን፣ እፅዋትን ከምድር በላይ ከሰማይ በታች የተፈጠሩትን ሁሉ የሚጠብቁ ናቸው፡፡
ኩፋሌ 2÷6-8

በ3ቱ ሰማያት ያሉት አስር አለቆችና መቶ ነገድ እነዚህ ናቸው፡፡ ሄኖክ 20÷38-42

Loading comments...