የዕሮብ ውዳሴ ማርያም

6 months ago
37

ረቡዕ የሚጸለይ አምላክን የወለደች የእመቤታችን የድንግል ማርያም ምስጋና። ሦስተኛ ክፍል።

፩ የምድር ሁለተኛ የሆንሽ ሰማይ ሆይ የሰማይ ሠራዊት (መላእክት) ንዕድ ነሽ ይላሉ።ድንግል ማርያም የምስራቅ ደጅ ናት።ሙሽራዋ ንጹሕ የሆነ ንጽሕት የሠርግ ቤት ናት።አብ በሰማይ አይቶ እንዳንቺ አላገኘምና አንድ ልጁን ላከው በአንችም ሰው ሆነ።ቅድስት ሆይ ለምኝልን።
፪ አምላክን የወለድሽ እመቤታችን ሆይ ትውልድ ሁሉ አንችን ብቻ ያመሰግኑሻል። ፫ የእግዚአብሔር ሀገር (ከተማ) ሆይ ነቢያት ድንቅ ድንቅ ነገርን ተናገሩልሽ፤ደስ የተሰኙ የጻድቃን ማደሪያ ሆነሻልና የምድር ነገሥታት ሁሉ በብርሃንሽ ይሄዳሉ። ሕዝቡም ሠራዊቶቻቸውም በብርሃንሽ ይሄዳሉ፤ማርያም ሆይ ትውልድ ሁሉ ያመሰግኑሻል።ካንቺ ለተወልደውም ይሰግዱለታል ያገኑታልም።ቅድስት ሆይ ለምኝልን።

፬ የዝናም ውሃ የታየብሽ የዕውነት ደመና አንች ነሽ።አብ የልጁ ምልክት አደረገሽ መንፈስ ቅዱስ አደረብሽ የልዑል ኃይል ጋረደሽ፤ማርያም ሆይ ለዘለዓለም የሚኖር የአብን ልጅ ቃልን የወለድሽልን መጥቶም ከኃጢአት አዳነን።ደስ የተሰኘህ ሆነህ ምሥራችን የተናገርክ መልአኩ ገብርኤል ሆይ የተሰጠህ ክብር ታላቅ ነው ወደኛ የመጣ የጌታን ልደት ነገርኸን ለድንግል ማርያም ጸጋን የተመላሽ ሆይ እግዚአብሔር ካንቺ ጋር ነውና ደስ ይበልሽ ብለህ አበሠርካት።
ቅድስት ሆይ ለምኝልን።

፭ ጸጋን አገኘሽ መንፈስ ቅዱስ አደረብሽ የልዑል ኃይልም ጋረደሽ (ጸለለብሽ) ማርያም ሆይ በውነት ቅዱሱን ወለድሽ ዓለምን ሁሉ የሚያድን መጥቶ አዳነን። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።

፮ አንደበታችን የድንግልን ሥራ ያመስግናል። ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዳዊት አገር ከእርስዋ ስለተወለደ አምላክን የወለደች ማርያምን ዛሬ እናመስግናት አሕዛብ ኑ ማርያምን እናመስግናት።እናትና ድንግል ሁለቱንም ሆናለችና።ርኩሰት የሌለብሽና የአብ ቃለ መጥቶ ካንቺ ሰው የሆነ ንጽሕት ድንግል ሆይ ደስ ይበልሽ።ነውር የሌለብሽ ፍጽምትና ጉድፍ የሌለብሽ ሙዳይ ሆይ ደስ ይበልሽ።ስለቀደመ ሰው አዳም ሁለተኛ አዳም የሆነ የክርስቶስ ማደሪያው የምትናገሪ ገነት ሆይ ደስ ይበልሽ። ከአባቱ ያልተለየ አንድ እሱን የተሸከምሽ ሆይ ደስ ይበልሽ። በክብር ጌጥ ሁሉ ያጌጠ እርሱ መጥቶ ሰው የሆነብሽ ንጽሕት የሠርግ ቤት ሆይ ደስ ይበልሽ። የመለኮት እሳት (ባሕርይ) ያላቃጠለሽ ዕፀ ጳጦስ ሆይ ደስ ይበልሽ።በኪሩቤል ላይ የሚቀመጠው ሰማያዊ መለኮትን በሥጋ የተሸከምሽ ገረድና እናት ድንግልና ሰማይ ሆይ ደስ ይበልሽ።ስለዚህ ንጹሓን ከሆኑ መላእክት ጋር በፍጹም ደስታ ደስ ተሰኝተን እናመስግን በሰማይ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን በምድርም ዕርቅ ይሁን እንበል ክብርና ምስጋና ጌትነት ያለው እርሱ አንችን ወድዋልና።
ቅድስት ሆይ ለምኝልን።

፯ ከቅዱሳን ክብር የማርያም ክብር ይበልጣል፣የአብን ቃል ለመቀበል በተገባ ተገኝታለችና።መላእክት የሚፈሩትን ትጉሆች በሰማይት የሚያመሰግኑትን ድንግል ማርያም በማኅፀንዋ ተሸከመቸው።ይህች ከኪሩቤል ትበልጣልች፣ከሱራፌልም ትበልጣልች ከሦስቱ አካል ላንዱ ማደሪያ ሆናለችና።
የነቢያት ሀገራቸው ኢየሩሳሌም
ይህች ናት።ለቅዱሳን ሁሉ የደስታቸው ማደሪያ ናት።በጨለማና በሞት ጥላ ውስጥ ለሚኖሩ ሰዎች ታላቅ ብርሃን ወጣላቸው።በቅዱሳን ላይ የሚያድር እግዚአብሔር እኛን ለማዳን ልዩ ከሆነች ድንግል ሰው ሆኗዋልና።ኑ ይህን ድንቅ እዩ። ስለተገለጠልን ምስጢር ምስጋና አቅርቡ።ሰው የማይሆን ሰው ሆኗልና። ቃል ተዋህዷልና።ጥንት የሌለው ሥጋ ጥንታዊ ቀዳማዊ ሆነ ዘመን የማይቆጠርለት መለኮት ዘመን ተቆጠረለት።የማይታወቅ ተገለጠ የማይታይ ታየ የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ በእርግጥ ሰው ሆነ።ትላንት የነበረው ዛሬም ያለው መቼም የሚኖረው ኢየሱስ ክርስቶስ እንሰግድለትና እናመስግነው ዘንድ አንድ ባሕርይ ነው።ቅድስት ሆይ ለምኝልን።

፰ ነቢዩ ሕዝቅኤል ስለ እርስዋ መሰከረ ድንቅ በሆነ ታላቅ ቁልፍ የተዘጋች ደጅ ምሥራቅ አየሁ አለ ከኃያላን ጌታ በቀር ወደ እርስዋ ገብቶ የወጣ የለም።ቅድስት ሆይ ለምኝልን።

፱ ኆኅትም ደጅም መድኃኒታችንን የወለደች ድንግል ናት።
እርሱን ከወለደች በኋላ እንደቀድሞ በድንግልና ኖራለችና።መጥቶ ምሕረት ከሌለው ጠላት እጅ ያዳነን ጌታን የወለድሽ ሆይ የማኅፅንሽ ፍሬ የተባረከ ነው፥ አንቺ ፍጽምትና የተባረክሽ ነሽ የዕውነት አምላክ በሆነ በክብር ባለቤት ዘንድ ባለሟልነትን አግኝተሻልና በምድር ላይ ከሚኖር ሁሉ ይልቅ ገናንነትና ክብር ለአንቺ ይገባል።የአብ ቃል መጥቶ በአንቺ ሰው ሆነ።ከሰው ጋርም ተመላለሰ። መሓሪ ይቅር ባይ ሰውን ወዳጅ ነውና በልዩ አመጣጡ አዳነን።ቅድስት ሆይ ለምኝልን።

Loading comments...