AFRICA:በወንጭፉ ፈረንሣይን ጉድ የሠራት | የ13 ዓመቱ ቡርኪ'ናዊ | Burkinabe boy shoots down French drone with slingshot

2 years ago
5

#Africa #Thomas_Sankara #Burkina_Faso  #imperialist_interventions #world #Drone_shoot_down #ethiooia #NoMore #viralyoutubevideo #ethiopia #Slingshot
" እውነትም አፍሪካ እየነቃች፣ እምቢ! እያለች ነው" የሚያስብል የ 13 ዓመቱ አፍሪካ-ቡርኪናዊ ታዳጊ ሕፃን ልጅ በትላንትናው እለት በፈረንሣይ ዘመናዊ ጦር ላይ የፈፀመውን እጅግ አስገራሚና አስደናቂ ጀብዱ እንነግራችኋለን፣  አብራችኹን ቆዩ።
"ይህንን በዓለም ዙሪያ የሚያዩ ሰዎች በ20ኛው ክፍለ ዘመን እንኳን - በእምነት ፣ በድፍረት እና ትክክለኛ በሆነ ምክንያት ዳዊት አሁንም ጎልያድን እንደሚያሸንፍ ይገነዘባሉ።"
ይኽንን የተናገሩት ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ናቸው። ጣልያን ኢትዮጵያን ለቆ እንደወጣ ፣ በአዲስ አበባው ቤተ መንግሥታቸው ለውጪ ጋዜጠኞች ባደረጉት ንግግር ላይ።
ከሰሞኑ የተቀጣጠለው የአፍሪካዊነት ስሜት ወራሪ ግፈኛዋ ፈረንሣይን ጨምሮ በርካታ ምዕራባውያንን ያስደነገጠ ክስተት እየሆነ ነው።
የሽብር ጥቃቶች በመጨመራቸው የተማረሩት የቀድሞ የፈረንሣይ ቀኝ ግዛት አካባቢ አገራት ዜጎች ፣ ፈረንሳይ ጦሯን እንድታስወጣ በመጠየቅ ላይ ናቸው።
ከሃገራቱም መካከል የፓን አፍሪካኒስቱ "ቶማስ ሳንካራ" ምድር የሆነችው ምእራብ አፍሪካዊቷ ቡርኪናፋሶና ሕዝቦቿ የኢምፔሪያሊስት ጣልቃገብነት በመቃወም የቀድሞ ቀኝ ገዣቸውን ፣ ወራሪዋን ፈረንሣይ በመቃወም ፣ ከሃገራቸው እንድትወጣ የተቃውሞ ሰልፍ ከጀመሩ በርካታ ቀናት ተቆጥረዋል።
ከተቃውሞ ድምፃቸውም መካከልም  "የቶማስ ሳንካራ ምድር  ኢምፔሪያሊስቶች ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነትን አትፈልግም።" የሚል ይገኝበታል።
ይኽ በሚሆንበት ወቅት የፈረንሳይ ወታደራዊ ኮንቮይ ቡርኪናፋሶ ውስጥ መገኘት ፣ በቡርኪናፋሶ ህዝብ ላይ ከፍተኛ ቁጣ ቀሰቀሰ
ወታደራዊ ኮንቮዩም በማገት ፈረንሣይ ጦሯን ከምድራቸው ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንድታስወጣ በመጠየቅና መንገድ በመዝጋትም ተቃውሟቸውን አጧጧፉት።

"ፈረንሣይ ሽብርተኞችን ትደግፋለች" ያሉ የካያ ከተማ ነዋሪዎች ቡርኪናውያን የፈረንሳይ የጦር ተሽከርካሪዎችን እና ኮንቴነሮችን አገቱ።

ካሣለፍነው ሣምንትም ጀምሮ በቡርኪናፋሶ ሰሜናዊ ማዕከላዊ ክልል ርዕሰ መዲና በሆነችው በካያ ከተማ (ቡርኪና ፋሶ) ትልቅ የፈረንሳይ ጦር ሎጅስቲክስ ኮንቮይ በወጣቶች ታግዷል ። ከፍተኛ ባለስልጣናት እንዲለቀቅ ሽምግልና ቢያደርጉም ፣ ወጣቶቹ መንገድ የዘጉባቸውን ቁሳቁስ ለማንሳት ፍላጎት አላሳዩም።

ከሠልፈኞቹ መካከልም አንዱ.....

"የፀጥታ ችግርን በመቃወም ሰልፍ ስናደርግ ከኮትዲቯር የፈረንሳይ ጦር ኮንቮይ ቡርኪናፋሶን አቋርጦ ወደ ኒጀር ሊሄድ መሆኑን ስናውቅ ለመከልከል ወስነናል ። ምክንያቱም ከፈረንሳይ ጋር የተፈራረምነው ስምምነቶች ቢኖሩም ሞት ማስመዝገባችንን ግን ቀጥለናል ፣ የቀጠናው ሃገሮችም ምንም አይነት የራሳችን የሆነ ትጥቅ ሳይኖረን ቆይተናል " ሲል የተቃውሞውን ምክንያት ያስረዳል።

ብዙ አፍሪካውያን አሜሪካ ኢትዮጵያ ውስጥ ጣልቃ መግባቷን በመቃወም ድምፅ እንደሆኑን እኛም ለቡርኪናፋሶ ወንድሞቻችን በየማህበራዊ ሚድያዎች ድምፅ እንድንሆናቸው በሚከተሉት ሃሽታጎች ትግላቸውን ተቀላቀሉ የሚለውን መልሕክታችንን እያስተላለፍን ፣

አስደናቂ ጀብዱ ወደፈፀመው የ13 ዓመቱ ታዳጊ ድርጊት እንለፍ.....

"የፈረንሳይ ጦር ውጣ"፣ "ነፃነት ለሳህል ቀጠና"፣
"ከእንግዲህ የፈረንሳይ ወረራ እና ወታደራዊ ኮንቮይ አያስፈልግም"፣

የሚሉ መፈክሮችን እያስተጋቡ በቡርኪና-ፋሶ 5ኛዋ ትልቋ ከተማ " ካያ" መግቢያ ላይ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች ተሰብስበውና መንገድ ዘግተው ተቃውሟቸውን በቁጣ በሚያሰሙበት ሰዓት፣

አንዲት ሰው አልባ በራሪ ፣ የፈረንሣይ ድሮን ሠልፈኞቹን ለማሸበርና ለኮንቮዮ መንገድ ለማስለቀቅ ከአናታቸው በላይ ከፍ ብላ በመብረር ታንዣብብ ያዘች ፣ 

በዚኽ ጊዜ የቶማስ ሳንካራ ጀግንነት በደሙ ውስጥ ያለ አንድ ታዳጊ በሰልፈኞቹ መካከል በጥድፊያ እየተሽሎኮለከ በልቡ ላቀደው አንድ አላማ በኪሶቹ ጠጠር በእጆቹ ወንጭፍ ባላ ይዟል ፣ በቁጣ ከሚጮኹት ሰልፈኞች መካከል ይኽን ጥቁር ብላቴና ልብ ያለው ግን አልነበረም ፣
ወትሮስ ይሕ ሕፃን ምን ሊፈይድ?
የዚኽ ብላቴና ሃገር ቡርኪናፋሶ በማዕድን ሃብት የናጠጠች ነች ፣ ነፃነቷን ከፈረንሳይ ካገኘች ከአመታት በኃላ ለሃገሩ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ብርሃን ሊሆን የሚችል "ቶማስ ሳንካራ" የተባለ መሪ አገኘች ፣ ወደ እድገት ማማ ወደ ብርሀን ጉዞ ስትጀምር ፈረንሣይ ተቆጣች! ፣

በባለ አእምሮው አፍሪካዊ ልሂቅ ቶማስ ሳንካራ መሪነት አስደናቂ እድገት ላይ የነበረችው ሃገር ቡርኪናፋሶ፣ በምዕራባውያን በተለይም በፈረንሣይ ሴራ ታላቁ መሪዋን አጣች ቶማስ ሣንካራ በግፍ ተገደለ ፣ ደሙም ደመ-ከልብ ሆነ አፍሪካ ማቅ ለበሰች ልቧ በሃዘን ተሰበረ።
ያ የቶማስ ሳንካራን ገድል እየሰማ ያደገው ጥቁሩ-ብርኪ'ናዊ  ብላቴና በሰዎች መካከል አልፎ ከሚፈልግበት ወሣኝ ስትራቴጂካዊ ቦታ ደረሰ....

ከአቅራቢያው ላሉት ሰዎች ኢላማውን እንዳይስት ለተቃውሞ የሚያወናጭፉትን እጃቸውን ለእይታው እንዲሰበስቡለት በጩኽት ትህዛዝ ሠጣቸው ፣ ሰዎቹም የሚያደርጉትን አቁመው ገለል ብለው ያላቸውን በማድረግ በግርምት ይመለከቱታል....

ሰው አልባዋ ድሮን በተገጠመላት ካሜራ አንድ አጠራጣሪ ነገር ያየች ይመስል ወዲህ ወዲህ ተንቀለቀለች።

ብላቴናው ጠጠሮቹን ከኪሱ አውጥቶ አንዲት ጠጠር መርጦ ፣ ጠጠሯ ኢላማውን እንዳትስት በደረቁ ከናፍርቱ ሳማት ፣ ከባለው ላይም ጠጠሯን አያይዞ በረዥሙ በመተንፈስ ወንጭፉን ወደኃላ ወጠረው.....
ይኽ ብላቴና ከላይ የለበሰው ልብስ አዳፋና የትልቅ ሰው ቲሸርት ነው፣  ሃገሩ በማዕድናት የናጠጠች ብትሆንም በምዕራባውያን በዝባዦች ሆድ ተርፎ እንኳን የሚከናነበው የሚበላውም የለምው ፣ ይኽ ጨቅላ በአፈር አቧራ የጠገበ ነጭነቱን ትቶ አቧራ ከለር የያዘ የነተበ ሱሪ አድርጓል።

እንኳን ለዚኽ ብላቴና የመላውን አውሮፓ የጥሬ እቃ እጥረትና ችግር መሸፈን የምትችለው ባለ አንጡሯ ሃብቷ ሃገሩ ፣ በምዕራባውያን ሴራ ከድህነት ወለል በታች ሆና በድህነት ውስጥ ተዘፍቃለች፣

የዚኽ ብላቴና እግሮች እንደነገሩ ክፍት ሸበጥ ተጫምተዋል፣  እግሮቹ አቧራ ጠግበው ደራርቀው ተሰነጣጥቀዋል።

ይኽ ብላቴና ትምህርትን ጨምሮ ለአንድ በሱ እድሜ ላለ ሕፃን ሊሟሉ የሚገባቸው መሰረታዊ እና ለኑሮ አስፈላጊ ነገሮች ለሱ ቅንጦት ናቸው።

ወንጭፍ ግን በእጁ ይዟል ፣ ነፃነት ያለ መራር ትግል እንደማይመጣ በትንሹ ልቡ ተረድቷል።
እልህ፣ ቁጭት፣ "እምቢ አልገዛም" ባይነት በመላው አፍሪካ ተቀጣጥሎ እዚኽ ጨቅላ ጋር ደርሷል፣

አባቶቹ ላይ የተጫነው የባርነት ቀምበር እሱም ላይ በእጅ አዙር በመጫኑ በኪሱ ጠጠር ድንጋይ በእጁ ወንጭፍ አንግቦ በልቡ ራዕይ ሰንቋል።
ብላቴናውና ድሮኗ ተፋጠዋል ፣ ምናልባት ድሮኗን ኦፕሬት የሚያደርጉ፣ የሚያንቀሳቅሷት ሰዎች ፣ "ጎልያዶቹ" ወንጭፉን ይዞ በካሜራ በሚያዩት ብላቴና ላይ እየተሳለቁ ፣ እየተዘባበቱበትም ይሆናል።

ይኽ ብላቴና ግን በድፍረት ፣በቆራጥነት እና በልበ-ምሉዕነት ባላውን ወጥሮ ፣ አንድ አይኑን ጨፍኖ ፣ ወንጭፉን አነጣጥሮ ድሮኗን ኢላማው ውስጥ ከተታት።

በድጋሚ በረዥሙ የነፃነት፣ የማሸነፍ ድል የማድረግ ትንፋሽ ተንፍሶ የተወጠረውን ወንጭፍ-ባላ ጠጠሯን ለቀቃት አንገቱን ወደ ላይ ቀና አድርጎ ፣ በአይኖቹ ጠጠሯን ይመራት ይመስል ይከተላታል፣

ጠጠሯ በፍጥነት ተምዘግዝጋ ሄዳ ሰው አልባዋን ድሮን መታቻት፣  ድሮኗ ከፍ ዝቅ መደ ወደ ግራ ወደ ቀኝ ተንተፋትፋ ተንገዳግዳ ተሽከርክራ ወደታች ተምዘግዝጋ ተፈጠፈጠች፣

ድሮኗ የቅርብ ጊዜ ስሪትና እጅግ ዘመናዊ የፈረንሳይ ሰው አልባ በራሪ ነበረች ።

የሚሆነውን በአንክሮ ይከታተሉ የነበሩ ብርኪናውያን ወደ ወደቀችው ድሮን በሩጫ ተመሙ፣ አይዋት በቁጣና በደስታ ድሮኗን በእግራቸው ረጋገጧት እያነሱ ከመሬት ደባለቋት አወደሟትና እልሃቸውን ከተወጡባት በኃላ ወደ ብላቴናው በሩጫ ተመለሱ....
ጥቁሩ ኩሩው ቡርኪና-አፍሪካዊው ብላቴና ግን ከቆመበት ሳይነቃነቅ በኩራት በድል አድራጊነት የሚሆነውን በንቃት ይከታተላል...ድንገት ሰዎቹ ብላቴናውን እንደማፈስ አድርገው አቅፈው ወደ ላይ ከፍ አድገው ይዘው፣  እየሳቁ ፣እየተደሰቱ " ዥግናችን" እያሉ ሕፃኑን ይዘው በድል አድራጊነት ጨፈሩ

ሕፃኑ "አሊዩ ሳዋዶጎ" በአቅሙ ለሃገሩ ተዋግቶ ፣ የቶማስ ሳንካራን መንፈስ ሕያው አድርጓልና።

የፈረንሳይ ጦር ኮንቮይም በመጨረሻ ወደ ኋላ በማፈግፈግ ወደ ዋጋዱጉ ዋና ከተማ በመመለስ አውሮፕላን ለመያዝ እና ወደ ኒያሚ ለመብረር ችሏል።

ከዋጋዱጉ በስተሰሜን ምስራቅ 103 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው የካያ ከተማ አቅራቢያ በፈረንሳይ ጦር ድሮን ላይ ወንጭፍ ተኩሶ ዘመናዊዋን ድሮን በመጣሉ የ13 አመቱ ታዳጊ የቡርኪናፋሶ ነዋሪ እንደ ጀግና እየተመለከቱት ደስታቸውንም እየገለጹ ፣ምስጋናቸውንም እያቀረቡለት እንደሆነ እየተነገረ ነው።

(ነጽሩ ወዘሠናየ አጽንዑ)

Loading comments...